የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፍሳሽ ቆሻሻ ውሃ ማከሚያ ማዕከል

Share this story

Posted on: Jul 19,2018

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፍሳሽ ቆሻሻ ውሃ ማከሚያ ማዕከል በብር 62,044,490.87 (ስልሳ ሁለት ሚሊየን አርባ አራት ሺህ አራት መቶ ዘጠና ብር ከ87/100 ሳንቲም) በሆነ ወጪ በመገንባት የካቲት 2008 ዓ/ም ተመርቆ በምህንድስና ቡድን መሪነት በይፋ ስራ የጀመረ ሲሆን ማዕከሉ በዋናነት ከዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች መኖሪያና ሌሎች መኖሪያ ያልሆኑ ህንጻዎች የሚወገድ የፍሳሽ ቆሻሻ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰሰብ ብሎም በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ችግር እንዳይፈጥር ብቻ ሳይሆን ተመልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን ታሳቢ አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡

ቀደም ሲል ከዩኒቨርሲቲው ይለቀቅ የነበረ የፍሳሽ ቆሻሻ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰሰብ ብሎም በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ የሽታ እንዲሁም ተዛማጅ የጤና ችግሮችን ያስከትል የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በእጅጉ ችግሩ መቀረፉ መምህር ሠለሞን ከምህንድስና ቡድን ክፍል አስታውቋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የፍሳሽ ቆሻሻ ውሃ ማከሚያ ሁለት የማጣሪያ መስመሮች ያሉት

ሲሆን እያንዳንዳቸው በሰዓት 64,800 (ስልሳ አራት ሺህ ስምንት መቶ) ሊትር የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን አሁን ላይ ካለው የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ብዛትና የሰው ኃይል አንጻር ብዙ የፍሳሽ ልቀት ባለመኖሩ አንደኛው መስመር ብቻ እየሰራ ይገኛል፡፡ ወደፊት ግን ዩኒቨርሲቲው እየሰፋ ሲሄድና ተማሪዎችን የመቀበል አቅሙ ሲጨምር ሁለቱም የማጣሪያ መስመር የሚሰሩበት ሁኔታ የሚፈጠር ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በአማካኝ 18,000 ሊትር በሰዓት እያጣራ መሆኑን መምህር ሠለሞን ተናግረዋል፡፡

እንዳጠቃላይ አሁን ላይ እየሰጠ ካለው አገልግሎቶች መካከል ተጣርቶ የተገኘውን ውሃና ማዳበሪያ ለዩኒቨርሲቲው የአትክልት ልማት አገልግሎት ማዋል፣ አለአግባብ የሚወጣ የውሃ ብክነት መቆጠብ  

እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰሰብ ብሎም በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚኖሩ ነዋሪዎች የአየር ንብረት ብክለትን በመከላከል በበሽታ እንዳይጠቁ ማድረግ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እና ዩኒቨርሲቲዎች ለልምድ ልውውጥ እንዲሁም ለተግባር ላይ ልምምድ ለሚመጡ ተማሪዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ስልጠናና ድጋፍ መስጠት በማዕከሉ የሚሰጣቸው ተጠቃሽ ተግባራት ናቸው፡፡

በተጨማሪም ወደፊት ለመስራት ከታሰቡ ስራዎች መካከል ከቆሻሻ ማከሚያ ማዕከል የሚወጣውን ባዮ ጋዝ ወደ ኃይል ማመንጫነት በመቀየር ለዩኒቨርስቲው አገለግሎት እዲሰጥ ማድረግ፣ በተጣራው ውሃ የዓሣ እርባታን መጀመር፣ የሚመረተውን ማዳበሪያ በአካባቢው ላሉና በግብርና ስራ ላይ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽና ተጠቃሚ እዲሆኑ ማድረግ፣ በአጠቃላይ የቆሻሻ ማከሚያ ማዕከሉን ግቢ ፓርክ በማድረግና በማስዋብ ለጎብኝዎችም ሆነ ለዩኒቨርሰቲው የተሻለ ገጽታና የአየር ንብረቱን ተመጣጣኝ ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ እንዲሁም በዋናነት በዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ሌሎች አካላት የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ማከናወን ይገኙበታል፡፡

በመጨረሻም ትኩረት ከሚገባቸው ነገሮች መካከል ቆሻሻ ማከሚያ ማዕከሉ የተለያዩ ባክቴሪያዎች ክምችት ያለበት በመሆኑ በዚህ ቦታ ለሚሰሩ ሰራተኞች በየጊዜው የደምብ ልብስና የጤና ክትትል ማድረግ፣ ለማዕከሉ አገልግሎት የሚሰጡ የላብራቶሪ ኬሚካሎች እጥረት መቅረፍ፣ ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በጊዜውና በአግባቡ ማቅረብ፣ ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ በቂ ሰራተኞችን ማሟላት ቸል የማይባሉ የዩኒቨርሲቲው ተግባራት መሆናቸውን መምህር ሠለሞን ከምህንድስና ክፍል አስገንዝቧል፡፡