በ2011 ዓ.ም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማርን ለማረጋገጥ ከድሬዳዋ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት ተደረገ

Share this story

Posted on: Oct 18,2018

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ2011 ዓ.ም ነባር ተማሪዎችን ከጥቅምት 9 -11/2011 ዓ.ም ድረስ እንዲሁም አዲስ ተመድበው የሚመጡ ተማሪዎችን ጥቅምት 15 - 18/2011 ዓ.ም ድረስ ለመቀበል ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዩኒቨርሲቲው ተመድበው የሚመጡ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልና ሠላማዊ የመማር ማስተማሩን ሂደት በተሳካ መልክ ለማስቀጠል ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዝና አባገዶዎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማና አካባቢ የማህበረሰብ ተወካዮችና ከፀጥታና ደህንነት ኃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባል የሆኑት ክቡር ኢብራሂም ኡስማንና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ያሬድ ማሞ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን ሠላም ለማስቀጠል መሰራት ባለባቸውና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተለየ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የኛ ተማሪዎች ስለሆኑ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ሠላም አግኝተው የሚጠበቀውን ዕውቀት ለማስጨበጥ ከእዚሀ በፊት እንዳደረግነው ሁላችንም የየድርሻችንን መወጣት 

አለብን በማለትና ለዩኒቨርሲቲው አመራርና ለከተማ አስተዳደሩ ይጠቅማሉ ያሉትን ምክርና አስተያየት እጅግ በሚማርክ መልኩ አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትና ክቡር ከንቲባው የተሰጡትን አስተያየቶች መቀበላቸውን በማስረዳት በቀጣይ የዩኒቨርሲቲውን ሠላም ከማስቀጠል አኳያ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው የጋራ መስማማት ላይ ደርሰው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡